በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን
ሦስቱ ዛፎች
የአራዊት መጠለያ ከሆነው ጥቅጥቅ ካለው ደን መካከል ከፍ ብለው የሚታዩ ሦስት ዛፎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ዛፎች ካሉበት ሆነው እንዳች ጠቃሚ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ዛፎች ወደ ፊት ምን መሆን እንደሚፈልጉ የልባቸውን ምኞት በግልጽ እየተነጋገሩ ነበር፡፡
“አኔ መቼስ” አለ አንደኛው ዛፍ “ፈጣሪዬ ቢፈቅድና ከአናጺዎች ምሳር ቢሠውረኝ ምኞቴ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነው፡፡” አለ፡፡ ሁለተኛው ዛፍ በመገረም “ዛፍ ካልተቆረጠና ለአንድ ሥራ ካልዋለ ዝም ብሎ ቢቆም አርጅቶ ከመውደቅ ሌላ ምን ትልቅ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል” ብሎ ጠየቀው፡፡ “አይ አንተ እንዳልከው አርጅቶ መውደቅ ሳይሆን የእኔ ምኞት የዕፅዋት ሁሉ ንጉሥ መሆንና ከፍ ከፍ ብሎ መታየት ነው፡፡
ሰዎች እኔን ሲያዩ እግዚአብሔርንና ነገትን እንዲያስታውሱ እፈልጋለሁ፡፡ አለ በተመስጦ፡፡ “ምን ዋጋ አለው እንዲህ ረዣዥሞች ሆነን ቆመን አንጺዎች አያዩንም ማለት መቼስ ዘበት ነው የአንተ ምኞት መቼስ ትንሽ ከበድ ያለ ሆነ” አለ ሶስተኛው ዛፍ በጥሞና የሁለት ወደጆቹን ንግግር ከሰማ በኋላ፡፡ ሁለተኛው ዛፍ ይህንን ተከትሎ ምኞቱን እንዲህ ሲል ተናገረ፡- “ የእኔ ምኞት እንኳን አለመቆረጥ አይደለም መቆረጥስን ልቆረጥ ነገር ግን የሚወስዱኝ አናጺዎች ወደ ቤተ መንግሥቱ የእንጨት ባለሙያዎች ወስደው እንዲሰጡኝ እፈልጋለሁ ከዚያም የንጉሡ ባለሙያዎች ለንጉሡ ዙፋን አድርገው ይሰሩኛል፡፡ የንጉሥ ዙፋን መሆን ማለት ደግሞ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ሲል ለወዳጆቹ የልቡን አጫወታቸው፡፡ “የእኛን ምኞት ሰማህ እስቲ የአንተን ደግሞ አጫውተን ለወደፊቱ ምን መሆን ትፈልጋለህ” አሉት ወደ ሦስተኛው ዛፍ እያተኮሩ “እኔ እንኳን የንጉሥ መሳፈሪያ መርከብ ሆኜ መሠራት ነው የምፈልገው ንጉሥና መኳንንቱ በእኔ እንዲሳፈሩ …..” እያለ ምኞቱን መዘርዘር ሲጀምር ከሩቅ የአናጺዎች ድምጽ ተሰማ፡፡ ዛፎች ተርበተበቱ በተለይም ከዛፎች ሁሉ ከፍ ብሎ መታየትና የዕፅዋት ንጉሥ የመባል ምኞት የነበረው ዛፍ በፍርሃት መወዛወዝ ጀመረ፡፡
አናጺዎቹ ተልከው የመጡ ይመስል ሦስቱን ዛፈች ለይተው ቆርጠው ጭነው ይዘዋቸው ሔዱ፡፡ “የዕፅዋት ንጉሥ ለመሆን ይመኝ የነበረውን አንደኛውን ዛፍ ይዞ የሔደው አናጺ በዕቃ ግምጃ ቤቱ ውስጥ አስቀመጠው፡፡ ምኞቱ እንደማይሳካ ገና ሲቆረጥ የታወቀው ቢሆንም በግምጃ ቤት ውስጥ ይቆለፍብኛል ብሎ አስቦ ስለማያውቅ ይህ ዛፍ ኀዘኑ ጸናበት ፈጣሪውንም አማረረ፡፡ ሁለተኛውን ዛፍ የወሰደው አናጺ ደግሞ ዛፉን ወስዶ ሳጥን አድርጎ ሠራው፡፡ ዙፋን ለመሆን የነበረውን ይህንን ዛፍ የከብቶች ምግብ የሚቀመጥበት ሳጥን ሆነ፡፡ ምንም እንኳን የንጉሥ ዙፋን ባይሆን ሳጥን ሆኖም ደህና ሳጥን ቢሆን አይጠላም ነበር፡፡ የተመኘውን ምኞት ተቃራኒ ሲገጥመውና በቤተ መንግሥት እውለለሁ ሲል ለዐይን በሚከፋ ለአፍንጫ በሚከረፋ በረት ውስጥ መገኘቱ የዚህን ዛፍ ልብ ሰበረው፡፡ ስለዚህ የምኞቱን ተገላቢጦሽ የሰጠውን ፈጣሪውን በተስፋ መቁረጥ አማረረ፡፡ ሦስተኛውን ዛፍ የቆረጠው አናጺ ደግሞ ዛፋ እንደተመኘው ለመርከብ ሠሪዎች ወስዶ ሰጠው፡፡ የንጉሥ መርከብ ለመሆን የጓጓው ይህ ዛፍ በደስታ ተውጦ ሠሪዎቹ መርከብ አድርገው እስኪሠሩት መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ይሁንና መርከብ ሠሪዎቹ የዛፋን ምኞት አልተረዱ ኖሮ የአሳ ማጥመጃ ታንኳ አድርገው ሠሩት፡፡ ስለዚህም ለጥቂት ጊዜ ተስፋው ለምልሞ እንዳልነበር ሁሉም ጉም እንደመዝገን ሆነበት፡፡ የንጉሥ መርከብ ሆኖ ሊጎበኘው የተመኘውን ባሕር ታንኳ ሆኖ ያለ ዕረፍት ከአሳ አጥማጆች ጋር ሊመላለስ ተገደደ፡፡ እርሱም እንደ ጓደኞቹ “ምነው አምላኬ ምን በደልኩህ” አለ፡፡ በአውግስጦስ ቄሣር ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ትዕዛዝ በወጣበት ጊዜ እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ጸንሳ ከነበረች ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ፡፡ በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ የበኩር ልጅዋንም ወለደች በመጠቅለያም ጠቀለለችው በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው፡፡ /ሉቃ 2፣3-6/ በተኛችበት ግርግም ውስጥ የተወለደው ሕፃን የተኛው ጭድ በተሞላ ሳጥን ውስጥ ነበር፡፡ ይህ ሳጥን የንጉሥ ዙፋን መሆን ይመኝ የነበረውና ሳጥን ሆኖ የተሠራው ዛፍ ነበር፡፡ “በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው፡፡ ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ ይገባ ነበር፡፡ እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር አንቅተውም፡ መምህር ሆይ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት፡፡ ነቅቶም ነፋሱን ገሰጸው ባሕሩንም ዝም በል ፀጥ በል አለው፡፡ ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ፡፡ እንዲሁ የምትፈሩ ስለ ምን ነው እንዴትስ እምነት የላችሁም አላቸው፡፡ እጅግም ፈሩና እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ፡፡” /ማር 4፡35-41/ ይህ ተዓምር የተፈጸመበት ታንኳ የንጉሥ መሳፈሪያ ለመሆን ይመኝ የነበረውና ታንኳ ሆኖ የተሠራው ዛፍ ነበር፡፡ ከፋሲካ በኋላ በዕለተ ዓርብ ከአንድ አናጺ ግምጀ ቤት የወጣን እንጨት አመሳቅለው ፍርድ አጓድለው ጌታን ሊሰቅሉበት አበጃጁት፡፡ ከዚህም በኋላ ይህንን መስቀል ጌታ ተሸክሞ እስከ ቀራንዮ ወጣ መስቀሉም በከበረ ደሙ በመታጠቡ ንጉሠ ዕፅዋት የዕፅዋት ንጉሥ /መስተበቁዕ ዘመስቀል/ ከዛፎች ሁሉም ከፍ ከፍ ያለ ሆነ ሰዎች ሁሉ እርሱን ሲያዩም ዛፍ ሆኖ እንደተመኘው እግዚአብሔርንና ነገትን ያስባሉ፡፡ የእነዚህ ሦስት ዛፎች ምኞትና ተስፋ የተበላሸና ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ነበር፡፡ ይሁንና ተስፋቸው ሲጠፋ እግዚአብሔር ሥራውን ጀመረ፡፡ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቋረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል” ኢሳ 10፡23 ዛፎቹ ተስፋ አድርገዋቸው ከነበሩት አናጺዎች ይልቅ ተስፋ ያላደረጉት እግዚአብሔር ምኞታቸውን ባላሰቡት መንገድ ፈጸመላቸው፡፡ ሁለቱ ዛፎች የምድራዊ ንጉሥ ዙፋንና መርከብ መሆን ተመኝተው ነበር የሰማይና የምድር ንጉሥ ሆኑ፡፡
“ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” ሰቆቃወ ኤር 3፡26፡፡ የዚህ ታሪክ መነሻ ሐሳብ “ the three trees” በሚል ርዕስ “Bishoys orthodox blog” በተሰኘ መካነ ድር ከተጻፈ ምሳሌ የተገኘ ነው፡፡ በሰውኛ ዘይቤ ዛፎች እንደሚናገሩ ተደርጎ የሚተርክ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስም ይገኛል፡፡(መሳ 9፡3 ፣ ዕዝራ 2፡15) ይህ ታሪክ በአስተማሪ ምሳሌነቱ እንጂ ስለ መስቀል ታሪካዊ አመጣጥ የሚጠቅስ አይደለም፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment