Tuesday, June 19, 2012

የመላዕክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል

ሚካኤል ማለት ‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው; ማለት ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ገናንነትና እሱን የሚመስል አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት ነው እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ ንጹሕ ርህሩህ ኃይል ረቂቅ ማነው መልሱ የለም ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል የስሙ ዘርፍ ሆነው የሚጨመሩ መጠሪያዎች አሉት እነዚህም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠውን የባለሟልነት ክብር የሚገልጹ ናቸው፡፡ ይኸውም መልአከ ኃይል፣ መጋቤ ብሉይ፣ መልአከ ምክሩ…ናቸው፡፡ መልአከ ኃይል የተባለው እግዚአብሔር በሱ አማካይነት ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ኃይሉን ስለገለጸ$ ዲያብሎስን ከነሠራዊቱ ስላሸነፈ ነው፡፡ መጋቤ ብሉይ የተባለበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከእግዚአብሔር እየተላከ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን የሠራ በመሆኑ ነው፡፡


መልአከ ምክር ወይም የእግዚአብሔር የምክሩ አበጋዝ የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔርን በምክሩ ይረዳዋል ለማለት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ለወዳጁ ለቅዱስ ሚካኤል ይገልጽለታል በሱም አማካኝነት ይሠራል ለማለት ነው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል በመጽሐፍ ቅዱስ


ቅዱስ ሚካኤል በዚህ ሁሉ ልዕልና ላይ ትሕትናን ደርቦ የያዘ በጸሎቱ ተማጽኖ በተራዳኢነት አምኖ ለሚለምነው ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ ከሠራዊተ አጋንንት ተንኰል የሚያድን መልአክ ነው፡፡ ወደ ቅዱስ መጽሐፍ ስንገባ ለቅዱስ ሚካኤል የተሰጠውን ክብርና ባለሟልነት እንዲሁም የሠራቸውን ሥራዎች እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ (ኢያሱ 5፡13-15) እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹እንዲህም ሆነ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፡፡ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፡፡ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን አለው፡፡ እርሱም አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ፡፡ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድን ነው አለው፡፡ የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን አንተ የቆምህበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው፡፡ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ ይላል፡፡ ይህን ጥቅስ ልብ ብለን ብናጤነው ለሌላው ሁሉ መርህ ይሆናልና ጥቂት ለማብራራት እንሞክራለን፡፡



እንዲሁም እግዚአብሔር ራሱ ለኢያሱ ‹‹…በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም ከሙሴ ጋር እንደሆነው እንዲሁ ካንተ ጋር እሆናለሁ አልጥልህም አልተውህም፡፡…›› (ኢያሱ 1፡1-9) በማለት ምን ያህል እንዳከበረው ያስረዳል፡፡ እስራኤላውያን አሞራውያንን በወጉ ጊዜ ቀኑ ስለመሸባቸው ከመደበኛው የተፈጥሮ ሕግ ውጭ ቀኑ እንደማይጨልምና መዓልቱ እንዲረዝም ኢያሱ በጸሎት ፈጣሪውን ስለጠየቀ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ቀኑን አስረዝሞ ከሰማይ በረድ አዝንሞ ጠላቶቻቸውን በማጥፋት የፈጸመውን አስደናቂ ተአምር እንዲህ ብሎ ጸፏል፡፡



‹‹...ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል (ልመና) የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም›› (ኢያ 10፡12-14) በማለት ተገልጿል፡፡ በጠቅላላው ከኢያሪኮ ጀምሮ ታላላቅ የአሕዛብ ምሽጐችን አፍርሶ አሕዛብን አጥፍቶ እግዚአብሔር ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ የማለላቸውን የተስፋይቱን ምድር ለልጆቻቸው ያወረሰ ኢያሱ ነው፡፡



ይህ የእስራኤል መሪ በእጅ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ የተገለጸለት ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን አላወቀም፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ከራሱ ወገን ወይም ከጠላቶቹ ወገን የሆነ አንድ ወታደር መስሎት ነበር፡፡ መልአኩ በሰው አምሳል ስለተገለጸለት አላወቀውም ነበር፡፡ ያነጋገረውም ያለ ፍርሃት ያለ ጭንቀት ያለድንጋጤ ወታደሮቹን እንደሚያነጋግር ዘና ብሎ ነው፡፡ ሆኖም ከመልአኩ የተሰጠው መልስ ታላቅ መሪና ነቢይ የሆነውን የኢያሱን አስተሳሰብ ለወጠው፡፡ ይኸውም ‹‹ከወገኖችህ ወይም ከጠላቶችህ አይደለሁም እኔ አሁን መጥቻለሁ" የሚለውን ቃል ሲሰማ ኢያሱ በፊቱ የቆመው ተራ ወታደር ሳይሆን የመላእክት ሠራዊት አለቃ ከሙሴ ሳይለይ የእስራኤልን ሕዝብ የሚጠብቅ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን ሲረዳ ለመልአኩ ክብር መስጠት ስለሚገባ የአክብሮት ስግደት ሰገደለት›› #ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድነው;$ በማለት በትህትና ጠየቀ፡፡ ጌታዬ አንተ ቅዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ለኢያሱ የምትነግረኝ ምንድነው; በማለቱ የእግዚአብሔርን ክብር ለፍጡር መስጠቱ አይደለም መላእክት ጌቶች ይባላሉ፡፡ ጌትነታቸውም የጸጋ ጌትነት ነው፡፡



ኢያሱ መልአኩን ጌታዬ ብሎ ከጠራው እኛማ ኃጢአተኞች ጌታዬ፤ ቀዱስ ሚካኤል ለኔ ለባሪያህ ጸልይልኝ መጥተህ አድነኝ…በማለት የአክብሮት (የጸጋ) ስግደት በመስገድ ብንለምነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጭ አልወጣንም፡፡ የፈጣሪን ክብር ለፍጡር አልሰጠንም፡፡ ተሳስታችኋል የሚለን ሰው ቢኖር እኛ አብነት ያደረግነው የእግዚአብሔር ወዳጅ ኢያሱን ስለሆነ ኢያሱም ተሳስተሃል ይባል፡፡ መልአኩም ኢያሱ ያቀረበለትን የአክብሮት ስግደትና ጥያቄ በመቀበል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መልእክት ነገረው፡፡ ኢያሱም ትእዛዙን ፈጸመ፡፡



እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ማለት መላእክትን ፈጥሮ የሚገዛ፣ የሚያዛቸው፣ የሚቀድሳቸው ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ የሚለው ከፈጣሪ በታች በመላእክት ላይ በፈጣሪ የተሾመ ማለት ነው፡፡ መላእክት አለቆቻቸውን ያከብራሉ፤ ለእነሱም ይታዘዛሉ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት ሁሉ አለቃ ስለሆነ ከትእዛዙ አይወጡም፤ ሠራዊተ መላእክት የሚያከብሩትንና የሚታዘዙለትን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እኛም እንደ ኢያሱ እናከብረዋለን እንታዘዘዋለን፡፡ መላእክትን ማክበርና መታዘዝ እንደሚገባ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ #በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክህን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፤ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት፤ አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፣ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፣ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፣ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፣ መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና…$(ዘጸ.23$2ዐ-22) በማለት ለሙሴ ተናግ ል፡፡ ይህ ቃል ለአንድ ጊዜ ብቻ ለሙሴና ለሕዝቡ ተነግሮ ያበቃ ሳይሆን እስከዛሬና ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ያን ጊዜ ሕዝበ እስራኤልን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻቸው አሕዛብን አጥፍቶ ምድረ ርስትን ምድራዊት ኢየሩሳሌምን እንዳወረሳቸው ዛሬም ይኸው መልአክ ቅዱስ ማካኤል እስራኤል ዘነፍስ የተባልን ህዝበ ክርስቲያንን ፊት ፊት እየመራ ጠላቶቻችን ሠራዋተ አጋንንትን እያጠፋ ምድረ ርስት ወደተባለች ሰማየ ሰማያት ያገባናል፡፡ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ለአዲስ ኪዳን ሕዝብ ምሳሌ ስለሆነ በታሪክነቱ ብቻ ተነግሮ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ኦሪት ሰም ሲሆን ሐዲስ ኪዳን ደግሞ ወርቅ ነውና፡፡


ይህ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ያወጣ፣ በበረሃ 4ዐ ዓመት የመራቸው፣ ምድር ርስትን ያወረሳቸው መሆኑን በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፊቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፡፡›› (ዘጸ.14፡15-20) በዚህ መሠረት እስራኤልን ይመራ የነበረው የእዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ እንዲሁም በኮሬብ ተራራ እግዚአብሔር ለሙሴ ሐመልማል ከነበልባል ተዋሕዶ በተገለጸለት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አልተለየም ነበር፡፡ (ዘጸ.3፡1-6፣ የሐዋ. 7፡3ዐ-34) በኦሪት የእግዚአብሔር መልአክ እየተባለ የሚጠራው አብዛኛውን ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ በድርሳነ ሚካኤልም ተጽፎ ይገኛል፡፡ (መዝ.33፡7) ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል) እግዚአብሔርን በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸዋል (በኢሳ.37፡36) ›› የእግዚአብሔር መልአክ(ቅዱስ ሚካኤል) መጣ፡፡ ከአሞራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ…›› በማለት ቅዱስ ሚካኤል ሕዝቅያስን እንዴት እንዳዳነው ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ሚካኤል ያልረዳው ቅዱስ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡



በዳን.1ዐ፡13 ‹‹የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ" በማለት የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ተገልጿል /ዳን.1ዐ፡21/፡፡ በዚሁ በትንቢተ ዳንኤል ም.12፡1 ላይ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል በማለት ታላቅነቱን፤ለሰው ልጆች ሁሉ በአማላጅነቱና በተራዳኢነት የሚቆም እንደሆነ በማያሻማ ቃል ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ ከክብሩ ያዋረደው ወደምድር የጣለው ቅዱስ ሚካኤል ቅዱሳን መላእክትን በመምራት ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ ጋር ስላደረገው ጦርነትና ስለተቀዳጀው ድል ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሀ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፤ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፡፡ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም፡፡ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው፡፡ ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀድሞው እባብ ወደ ምድር ተጣለ፡፡ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ…" (ራእ.12፡7-9) ዛሬም ቅዱስ ሚካኤል ሰዳዴ አጋንት አጋንንትን የሚያሳድድ በመሆኑ ከሰይጣንና ከሠራዊቱ መከራ እንዲያድናቸው በጸሎት ለሚለምኑት በቃል ኪዳኑ ለሚማፀኑት ሁሉ ፈጥኖ እየደረሰ ይታደጋቸዋል፡፡ በዙሪያቸው እየከተመ አጥር ቅጥር ሆኖ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድናቸዋል (መዝ.33፡7)፡፡



በመልእክተ ይሁዳ ቁ.9 ‹‹የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም$ በማለት ቅዱስ ሚካአል ዲያበሎስን እንኳ እግዚአብሔር ይፍረድብህ ከማለት በቀር ሌላ ቃል አለመናገሩ ታጋሽነቱን ያሳያል፡፡



የቅዱስ ሚካኤል ክብር



በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅዱስ ሚካኤል ለማንም ያልተሰጠ እጅግ ታላቅ የሆነ ክብር እንደተሰጠው ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ይኸውም በዕለተ ምጽአት ጌታችን ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በክበበ ትስብአት በግርማ መለኮት በሚመጣበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሙታን ላይ ሥልጣን የተሰጠው ለዚሁ ለኃያሉ መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ ገልጾታል፡፡ እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ ሁላችን አናንቀላፋም፡፡ ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን ይላል(1ቆሮ.15፡51-52) ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ‹‹በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስ የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ…›› (1ተሰ..4፡15-16) በማለት በዕለተ ምጽአት ምን ያህል ክብርና ጌትነት እንደሚሰጠው ይገልጽልናል፡፡

የቅዱስ ሚካኤል በዓል


የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየወሩ በ12 መታሰቢያውን እንድናደርግ አዘውናል፡፡ዛሬ ሰኔ 12 የምናከብርበት ምክንያት ግን

1, የቅድስ አፎሚያን ዕረፍት

አፎምያ የምትባል በሐይማኖትና በምግባር ጸንታ በመገኘቷ የጽድቅ ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን ራሱን የብርሃን መልአክና መንፈሳዊ አባት መስሎ በተደጋጋሚ ከሐይማኖት ጎዳና እንድትወጣ ተፈታትኖታል። እርስዋ ግን «በሰይጣን እንዳንታለል የእርሱን ሃሳብ አንስተውምና» 2ቆሮ 2፡11 እንደተባለ በሰይጣን ተንኮል ሳትሳሳት በእግዚአብሔር ላይ በነበራት የጸና እምነትና በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ፍጹም በመታመኗ በሰይጣን የቀረበላትን ፈተና በድል አድራጊነት በዛሬው ቀን ሴኔ 12 በክብር አርፋለች።

2, የባህራንን የሞት ደብዳቤ ወደሕይወት የቀየረበት ዕለት ነው፡፡

የባህራን ታሪክ

በእስክንድርያ ሃገር እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበር በየወሩም የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ያደርግ ነበር ጎረቤቱም አንድ ክፉ ባለጠጋ ነበር። ይህ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ በሚያደርግበት ጊዜ ያ ባለጠጋ ግን በሰውየው ላይ ይዝትበት ነበር። ይህ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውም እንደሚሞት ባወቀ ጊዜ ለባለቤቱ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር እንዳታቋርጥ ነገራት በተለይም በህዳር 12 እና በሰኔ 12 በልዩ ዝግጅት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንድታደርግ አዘዛት።ከዚህ በኋል ያ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው አረፈ እርሱ ባረፈበት ወራት ባለቤቱ ፀንሳ ነበር የመውለጃዋ ቀን ደርሶ በምጥ ተያዘች መከራውም እጅግ ፀናባት ወደ ቅዱስ ሚካኤል አሰምታ ጮኸች ይህንንም እንደተናገረች ያለችበት ቤት በብርሃን ተሞ ላ ከጭንቋ ድና መልኩ ያማረ ወንድ ልጅንም ወለደች የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወረደ የወለደችውንም ህፃን ባረከው እናቱንም እንዲህ አላት “” ይህ ብላቴና ምህረት ከሌለው የጎረቤትሽን የዚህንባለፀጋ ገንዘብ ሃብቱን ንብረቱን ሁሉ ይወርሳል ብሏል እግዚአብ ሔር “” አላት ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ያ ባለፀጋ በሴቲቱ ቤት መስኮት በኩል ሆኖ ይመለከት ነበርና ይህን ሲሰማ ተቆጣ ብላቴናውንም ለመግደል ምክንያትን ይፈልግ ጀመር ከእለታት አንድ ቀንም እድሜው 10 ዓመት ሲሆን የእናቱ ገንዘብ አለቀ ያም ባለጸጋ የሴቲቱን ችግር አይቶ ልጅሽን እንዳሳድገው ስጪኝ እኔ አበላዋለሁ እኔ አለብሰዋለሁ ላንቺም 20 ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ አላት ያችም ሴት ከባለጸጋው ይህንን ስትሰማ ተቸግራ ስለነበር ደስ አላት ባለጸጋውም 20 ወቄት ወርቅ ሰጣት እርሷም ልጅዋን ሰጠችው ከዚህ በኋላ ብላቴናውን እንዴት መግደል እንዳለበት ያሴር ጀመር በብላቴናው ቁመት ልክ ሳጥን አሰርቶ ብላቴናውን ከሳጥን ከቶ ቆልፎ ከባህር ውስጥ ወረወረው ያ ሳጥን ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ የባህር ወደብ ደረሰ አንድ ሰውም በጎቹን አሰማርቶ እየጠበቀ ሳለ ከባህሩ አጠገብ አንድ ሳጥን ከባህሩ ላይ ተንሳፎ አየ ሳጥኑንም ከባህሩ ካአወጣው በኋላ እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ያሰላስል ጀመር ሳጥኑንም ወደ ቤቱ ይሆት ሔደ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ይህንን ሰው ዳግመኛ ወደ ባህር እንዲሄድ አዘዘው ፈጥኖም ወደ ባህር ሔደ በዚያም አንድ አሣ አጥማጅ አገኘ ይህም ሰው ለአሣ አጥማጁ መረቡን ስለእርሱ እንዲጥለው አዘዘው አጥማጁም እንዳዘዘው አደረገ ትልቅም አሣ ያዘ ለአሣ አጥማጁም ዋጋውን ሰጥቶ ወደ ቤቱ ይዞት ተመለሰ። አሣውንም ለማዘጋጀት ፈልጎ ሲቀደው የሳጥኑን መክፈቻ አገኘ የእግዚአብሔ ር ስራው ድንቅ ነውና ሳጥኑን ለመክ ፈት ሲሞክር ፈጥኖ ተከፈተ በሣጥኑ ውስጥም ያ ክፉ ባለጸጋ የጥለው ብላቴና አገኘ የበግ ጠባቂው ፈጽሞ ተደነቀ ልጅም ስላልነበረው እጅግ በጣም ተደሰተ ብላቴናውንም ከባህር ስላገኘው ባህራን አለው። በግ ጠባቂውም ልክ እንደ ልጁ አድርጎ አሳደገው ተንከባከበው። ከብዙ ጌዜ ቆይታ በኋላ ያ ጨካኝ ባለጸጋ ለንግድ ወደ ሩቅ ሃገር ለመሔድ መንገድ ጀመረ ከአንድ የባህር ወደብ ሲደርስ ፀሐይ ጠለቀችበት በባህሩም አጠገብ ባህራንን ያገነውን የበጎች ጠባቂ አገኘው ወደ እርሱም ተጠግቶ ማደሪያ ካለው እንዲያሳድረው ለመነው። የበግ ጠባቂውም እንግዳውን በክብር ወስዶ አሳደረው በቤቱም ሳሉ በግ ጠባቂው “” ባህራን ፣ ባህራን”” ብሎ ሲጣራ ያ ባለጸጋ ሰማና ልጅህ ነው? ሲል ጠየቀው በግ ጠባቂውም አዎን ልጄ ነው ህፃን ሳለ ከባህር ስላገኘሁት ስሙን ባህራን አልኩት አለው። ባለጸጋውም ወደባህር የጣለው ህጻን መሆኑን አውቆ በልቡ እጅግ ተበሳጨ ዳግመኛም ብላቴናውን እንዴት መግደል እንዳለበት ያሴር ጀመር ለበግ ጠባቂውም ይህንን ብላቴና ወደቤቴ ልላከው የረሳሁት እቃ ስላለ ያምጣልኝ ለአንተ 20 ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ አለው። የበግ ጠባቂውም ስለሚሰጠው ወርቅ ተደስቶ ባህራንን ጠርቶ ይህ የከበረ ሰው ወደቤቱ ሊልክህ ነውና ተላከው አለው። ባህራንም ትዕዛዙን በእሺታ ተቀብሎ ባለጸጋው የሰጠውን ደብዳቤ ይዞ መንገድ ጀመረ ባለጸጋው የፃፈውም ደብዳቤ እንዲህ ይል ነበር “” ይህ ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ ያመጣት ስሙ ባህራን የተባለውን ሰው ገድለህ ከጉድጓድ ጣለው ይህንንም ነገር ማንም እንዳያውቅ ብሎ ወደ ሱሙ ላከ፡ በደብዳቤውም መጨረሻ በመካከላቸው ያለውን ምልክት ፃፈበት። ባህራንም የሞቱን ደብዳቤ በእጁ ጨብጦ ወደተላከበት ሃገር ሄደ። በመንገድም ሳለ ቅዱስ ሚካኤል የንጉሱን መልዕክተኛ መስሎ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ወደ ባህራን መጣ እንዴት አደርክ? ወዴት ትሄዳለህ? ምንስ ይዘሃል? አለው። ባህራንም አንድ ባለጠጋ ወደቤቱ ልኮኛል የመልዕክትም ደብዳቤ ይዣለሁ አለው። ቅዱስ ሚካኤልም ደብዳቤውን አሳየኝ አለው ባህራንም ያቅዱስ ሚካኤልን ግርማውን ፈርቶ በእጁ ያለውን ደብዳቤ አሳየው ቅዱስ ሚካኤል እፍ ሲልበት ያባለፀጋው ደብዳቤ ተቀየረ እንዲም ሆነ “” እኔ ባለጸጋው እገሌ ነኝ ይህን ደብዳቤ የያዘው ሰው ወደ እናንተ ልኬዋለሁ እገሊት የምትባል ልጄን ዳሩት ገንዘቤን ሁሉ ሰጥቼዋለሁ በቤቴ የወደደውን ያድርግ እኔ በንግድ እቆ ያለሁና አትጠብቁኝ በእኔና በእናንተ መካከል ይህ ምልክት ነው”” የሚል ነበር። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ባህራንን ወደ ባለጸጋው ቤት ሂድ እኔ መንገድ እንዳገኘሁህ አትናገር ይህንንም ደብዳቤ ለታዘዝከው ስጥ አለና ከፊቱ ተሰወረ። ባህራንም ወደተላከው ሹም ሄደ ደብዳቤውንም ሰጠው ሹሙም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ በንጉሱና በእርሱ መካከል ያለውን ምልክት አየ።ከዚህ በኋል ለባህራን ሰርግ ታላቅ ዝግጅት ተደረገ ከባለጸጋውልጅ ጋር በእግዚአብሔር ቤት በሥርዓተ ተክሊል አጋቡት የሰርጉንም ደስታ ምክንያት በማድረግ 40 ቀን ተቀመጡ ሰርጉም ካለፈ በኋላ ያ ባለጸጋ ወደቤቱ ተመለሰ በመንደሩም የደስታ ድምጽ ሰምቶ ምንድነው የምሰማው ብሎ ጠየቀ ሰዎችም ባህራን በሚል ልጅ ደብዳቤህ ስለደረሰን ልጅህን እንዲያገባ ሃብትህን ንብረትህን እንዲወርስ ስላዘዝከን ትዕዛዝህ ሁሉ ተፈጽሟል እንሆ ደስታ ስናደርግ 40 ቀን አለፈ አሉት። በዚህን ጊዜ ያ ክፉ ባለጸጋ በታላቅ ቃል ጮኸ ከመሬት ላይ ወድቆ ሞተ። /ድርሳነ ሚካኤል ዘወርሃ ሰኔ/



በቅዳሴያችን ‹‹ተውህቦ ምሕረት ለሚካኤል፤ ለሚካኤል ምሕረት (ይቅርታ ርኀራኄ) ተሰጠው ይላል፡፡ ነቢዩ ሄኖክም ምሕረት ለሚካኤል መሰጠቱን ገልጿል፡፡ ትሕትናውን ታዛዥነቱን አስረድቷል (ሄኖክ. 6፡5, 10፡12)፡፡


የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ለሰው ሁሉ የሚራራና ስለ ሰው ልጆች ሳያቋርጥ ወደ ፈጣሪው የሚለምን ርኀሩኀ ትሑት የሆነው ኃያሉ ቅዱስ ሚካኤል የሠራውን ሥራ የክብሩን ገናንነት ጽፈን ለመጨረስ ስለማይቻለን በዚሁ እናበቃለን፡፡ ጸሎቱ እና በረከቱ፣ ተራዳኢነቱም በእኛ በሁላችን ለዘላለሙ ይሁን፡አሜን፡፡


1 comment: