ዳንኤል ክብረት
http://www.danielkibret.com/2011/09/blog-post_19.html#morehttp
ቀደምት አበው እና እማት የሰይጣንን ማንነት በሚገባ ከማወቃቸው የተነሣ ሰይጣን መዋጋት እና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሰይጣንን ራሱን ያታልሉት ነበር፡፡ ይህም መንፈሳዊ ብቃታቸው እና ዕውቀታቸው የቱን ያህል ይደርስ እንደነበረ ከሚመሰክሩት ነገሮች አንዱ ነው፡፡
የትምህርተ ኅቡዓት መተርጉማን «ሰይጣን የተነገረውን እንጂ የታሰበውን አያውቀውም» ይላሉ፡፡ ሰይጣን የሚችለው በሰው ልቡና የታሰበውን መገመት ብቻ ነው፡፡ በሰው ልቡና የተመላለሰውን ማወቅ ስለማይችል ሰዎች የልባቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል፡፡ ሔዋንን ስለ ዕጸ በለስ ያንን ሁሉ የጠየቃት ለማወቅ ወይንም ለመረዳት ፈልጎ ሳይሆን ሥላሴ በሔዋን ልቡና የጻፉትን ነገር ማወቅ ስላልቻለ ነው፡፡ ሔዋን ስትናገር ግን ሃሳቡን ዐወቀ፡፡ ዐውቆም ዝም አላለም ጠልፎ የሚጥልበትን ወጥመድ አዘጋጀ፡፡
እናቶቻችን ወደ ቅዱሳት መካናት ለመሳለም ሲሄዱ «ላሊበላ፣ አኩስም፣ ግሼን ልሄድ ነው» አይሉም ነበር፡፡ «እንጨት ልሰብር፣ ውኃ ልቀዳ፣ ዘመድ ልጠይቅ» እያሉ ነበር የሚጓዙት፡፡ ይህም ሰይጣን በልቡናቸው ያለውን ተረድቶ ዕንቅፋት እንዳያመጣባቸው ነው፡፡
ይህንን የሰይጣን ስንፍና ከሚያውቁ አበው መካከል አባ ሉቃ እና አባ ታድራ ያደረጉትን ከመጽሐፈ መነኮሳት አንዱ የሆነው መጽሐፈ ፊልክስዮስ ክፍል ፬ ተስእሎ ፶፮ ገጽ 91 ላይ እንዲህ ይነግረናል፡፡
በአንድ ገዳም ውስጥ አባ ታድራ እና አባ ሉቃ የሚባሉ መነኮሳት ነበሩ፡፡ እንጸናለን ብለው የመጡ ብዙ መነኮሳትን ሰይጣን ከበኣታቸው ሲያስወጣቸው ተመለከቱና እንዲሁ ውስጥ ለውስጥ ተግባቡ፡፡ «በቀጣዩ ክረምት ከበኣታችን ወጥተን በበረሃ ለብቻችን እንጋደላለን፤ በዚያም ሰይጣንን ድል እናደርገዋለን» ተባባሉ፡፡ ሰይጣንም እውነት መስሎት እነርሱን ከበኣታቸው ለማውጣት የሚያደርገውን ፈተና ተወው፡፡ በበረሃም ይጠብቃቸው ጀመር፡፡
ክረምት በደረሰ ጊዜም «አሁንማ በክረምት እንዴት እንሄዳለን፤ በጋ ሲወጣ በረሃ ወርደን ሰይጣንን እንቀጠቅጠዋለን፣ እስከዚያ ዝም ብለን እንቀመጥ» ተባባሉ፡፡ ሰይጣንም እውነት መስሎት ፈተናውን ሁሉ ትቶ በጋ እስኪደርስ ጠበቃቸው፡፡ በጋም በደረሰ ጊዜ «ወደ በረሃ እንሄዳለን ተባብለንኮ ሰነፍን፣ ምን ይሻላል፤በቃ በክረምት እንሄዳለን» ተባባሉ፡፡
እንዲህ እያሉ ሰይጣንን ሃምሳ ስድስት ዓመት ዘበቱበት፡፡ በዚህም የተነሣ የመልክአ ሥላሴ ደራሲ እንዲህ የሚል አርኬ ደረሰላቸው
ሰላም ለአክናፊክሙ እሳታውያን አክናፍ
እለ በማእከል ሀለው ወእለ ሀለው በጽንፍ
አለብወኒ ሥላሴ ቀትለ መስተጋድል መጽሐፍ
ከመ ወትረ ይትዋሥአኒ ትምይንተ ሉቃ ትሩፍ
ወጉሕልተ ታድራ ምስሌየ ይዛዋዕ በአፍ፡፡
በጎ ነገሮችን ከሰው ተማክሮ መሥራት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ቆራጥነትን የሚጠይቁ፣ ፈተናም የሚበዛባቸውን መልካም ነገሮችን ከመሥራት በፊት ማውራት ግን በራስ ፈቃድ መከራ መጋበዝ ነው፡፡ አበው እንዳሉት ሰይጣን የተነገረውን እንጂ የታሰበውን አያውቅም፡፡ ስለዚህም ስለምናስበው ነገር ሁሉ በየአጋጣሚው እንድናወራ ያደርገናል፡፡
ሥራን አንደበት ከሚገልጠው ራሱ ሥራው ራሱን ቢገልጥ እንዴት የተሻለ ነው፡፡ ብዙ እያወሩ ጥቂት ከመሥራት፣ ምንም ሳያወሩ ብዙ መሥራት እንዴት መልካም ነው፡፡ ሞያ በልብ ነው ይላል የሀገሬ ሰው፡፡
በየትዳሩ፣ በየማኅበሩ፣ በየጉባኤው፣ በየአጥቢያው ፈተና ከሚበዛባቸው ምክንያቶች አንዱ ይኼ ሊሆንስ ከቻለ? ሁሉንም ነገር ለሰይጣን ስለምንነግረው፡፡ ባል እና ሚስት ተያይተው ብቻ የሚግባቡባቸውን መንገዶች ገንዘብ ማድረግ አለባቸው፡፡ የምናስበውን ሁሉ አናውራ፡፡ በልቡናችን ተቀምጦ በተግባር ብቻ መገለጥ ያለበትን እንለይ፡፡
ኮሚቴ ሲበዛ፣ ስበሰባ ሲበዛ፣ ውይይት ሲበዛ፣ ሰው ሲበዛ በዙ ጊዜ መንፈሳዊ ሥራ መሠራት ከባድ ይሆናል፡፡ መሰናክሉም ይበዛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ ጋር አጅሬም አብሮ ሳይሰበሰብ አይቀርም፡፡
ሴት የበዛበት ወጥ እና ወሬ የበዛበት መንፈሳዊ ሥራ ሁለቱም ይበላሻሉ፡፡
እስኪ ከወሬ ተግባር ይቅደም፡፡ የነ አባ ትዳራን እና የነ አባ ሉቃን ነገር ባንረሳው መልካም ነው፡፡
No comments:
Post a Comment